Qerro Media Service - QMS's Post

ሠራዊቱና ሕገ-መንግሥቱ
==================
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 87 መሠረት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አሠራርና የኢትዮጵያ የመከላከያና ደህነት ፖሊሲ የሚመራባቸው መርሆዎች የሚከተሉት ናቸው፦

1. ሕዝባዊነት (87(1)):
------------------------------
ሠራዊቱ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ የተውጣጡ አባላት የሚገኙበት ተቋም በመሆኑ የእራሱንና የአገሪቱን ሕብረብሔራዊነት ያንጸባርቃል፣ ሊያንጸባርቅም ይገባል። የሁሉንም መብት አክብሮ፣ የሁሉንም ሉዓላዊነትና የሁሉንም የጋራ አገራዊ ጥቅም ለማስከበር በደሙና በነፍሱ መስዋዕት ለመሆን የተሰለፈ አካል ነው። ይሄ ሠራዊት ጥሪው፣ አገርን ከውጭ ጠላት፣ የሕዝቦችን የሥልጣን ባለቤትነት (በሕገ-መንግሥቱ ተቀዳሚ መርህ የሆነውን የብሔሮች ሉዓላዊ ሥልጣን) ከውስጥ አጭበርባሪዎችና ከሃዲዎች መጠበቅ ነው(87(3)))። የኢትዮጵያ ብሔሮች ሠራዊት እንደመሆኑ፣ በውጭም ሆነ በውስጥ እንቅስቃሴው ሁሉ ብሔሮቹን በበቂ ደረጃ የመወከል ቁመና ሊላበስ ይገባዋል። ለዚህም ነው በተቻለ መጠን የሁሉም ብሔር አባላት ተዋጽኦ እንዲታይበት የሚበረታታው። ለዚህም ነው፣ ሠራዊቱ በአንድ ወይም በሌላ ብሔር ላይ ፖለቲከኞች የሚያውጁት ፖለቲካዊ ጦርነት ላይ መሳተፍ የሌለበት፣ እንዲህ ያለውንም ተግባር ለማስቆም፣ በፍጥነትና በብቃት መንቀሳቀስ የሚገባው።

2. ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት (87(2))፦
---------------------------------------------------
ሠራዊቱ፣ ሥራውን ሙያዊ በሆነ አኳኋን ብቻ የሚፈጽም ቢሆንም፣ ፖለቲካዊ ተጠያቂነቱንም ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ ለሚፈጽማቸው ኦፕሬሽኖች ስኬት የሚያስፈልጉ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ አቅርቦቶችን ለማቀላጠፍም ሲባል (ለሠራዊቱ አባላት እና ለአስተዳደር ሠራተኞቹ አስተዳደራዊ ፍትህ ለማቀላጠፍም ጭምር)፣ በካቢኔው ውስጥ ሠራዊቱን በሚወክል ሲቪል የሆነ የመከላከያ ሚኒስትር ይመራል። ይህ የሲቪልያን ተጠሪነት መርህ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩን ስንሾም፣ ፖለቲካውን ከጦሩ፣ ጦሩንም ከወገንተኛ ፖለቲካ ለመከላከል እንዲያስችል ታስቦበትና ጥንቃቄ ተደርጎበት እንዲፈጸም ግድ ይለናል። ሲቻልም--በአንዳንድ አገሮች እንደሚደረገው--አብዛኛው የመስሪያ ቤቱ ሥራ፣ በቋሚ ምኒስትር ተጠሪዎች (በ Permanent Secretaries) እንዲመራ የሚደረገው፣ ከዚህ መርህ ማዕከላዊነት የተነሳ ነው።

3. የአገር ሉዓላዊነትን የመጠበቅና ሕገ-መንግሥታዊ ግዳጅን የመወጣት ግዴታ (87(3))
--------------------
የሠራዊቱ ተቀዳሚ ተግባር፣ የአገርን ሉዓላዊነት ከውጭ ጠላት መከላከል ነው። አገርንና ወገንን ከጥቃት፣ ድንበርን ከወረራ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ከተቀናቃኝ የመጠበቅ ግዴታ ዘመን-ተሻጋሪ፣ ከአገር ውስጥ ፖለቲካው መለዋወጥ ጋር የማይለዋወጥ ቋሚ የሠራዊቱ ግዴታ ነው። ይሄንን ግዴታ ለመወጣት ደግሞ ከየትኛውም የመንግሥት ሥልጣንን ከተቆናጠጠ ፓርቲ አስፈላጊው ፖለቲካዊ-ስትራቴጂካዊ አመራር፣ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፍ፣ እና አስተዳደራዊ እገዛ ሊደረግለት ይገባል።

ከዚህም ባሻገር፣ ሠራዊቱ፣ በወረርሽኝ፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ ወይም በሕግና ሥርዓት መፍረስ ምክንያት በአገር ውስጥ ችግር ተፈጥሮ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት (እና ተቋማቱ) ለአደጋ ሲጋለጥ (በአንቀጽ 93 መሠረት) በፖለቲካ አመራሩ የሚሠጠውን የአስቸኳይ ጊዜ ሥራ እንዲሠራ ይገደዳል። ይሄን ሥራ ሲሰራም፣ ሥልጣኑ፣ በተገቢው መንገድ በሚወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የተገደበና ለነዚህም የሚገዛ ይሆናል።

4. ሕገመንግሥታዊነት 87(4)
---------------------------------------
የመከላከያ ሠራዊቱ በማንኛው ጊዜ እና በማናቸውም ሁኔታ፣ ለሕገመንግሥቱ ታማኝ ይሆናል። በመሆኑም፣ ሕገመንግሥቱን ያከብራል፣ ለሕገ-መንግሥቱ ይታዘዛል።

የሠራዊቱ አመራርም፣ ሕገ-መንግሥቱ ፣ የእንቅስቃሴው ሁሉ ማዕከል፣ የመኖሩ ምክንያት፣ እና የህልውናው መሠረት መሆኑን በመገንዘብ ሁኔታዎችን በንቃት መከታተል ይገባዋል።

አመራሩ እንዲፈጽምና እንዲያስፈጽም የሚታዘዛቸው ትዕዛዛትም ይዘታቸውም ሆነ አወጣጣቸው ሕገ-መንግሥታዊ መሆን ይገባቸዋል። በተጓዳኝ፣ አመራሩ፣ Commander's responsibilityን ምክንያት በማድረግ ብቻ፣ በግልጽ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ የሆነ ትዕዛዝን የመፈጸም ግዴታ የለበትም።

የፖለቲካ አመራሩ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን፣ አገራዊ ሉዓላዊነትን፣ እና አገራዊ ጥቅምን ለአደጋ የሚያጋልጥ ተግባራትን ሲፈጽም (ለምሳሌ፣ በአገር ጥቅም ላይ የሚያሴር የሚስጥር ስምምነት ሲስማማ፣ ክህደት ሲፈጽም፣ የመንግሥት ሚስጥርን አላግባብ በድብቅ እንዲወጣና ለጠላት እንዲደርስ ሲያደርግ፣ የውጭ የጸጥታ ኃይሎችን አስርጾ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ፣ የውጭ ኃይሎችን በመጠቀም የዜጎችን ህይወት፣ መብትና ጥቅም ለጥፋት ሲያጋልጥ፣ ወዘተ)፣ አመራሩን አለመታዘዝ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊና ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የማስቆም ኃላፊነት አለበት።

5. ከወገንተኛ ፖለቲካ ገለልተኛ የመሆን ግዴታ (87(5))
---------------------
ሠራዊቱ ሁል ጊዜም፣ ከወገንተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ እራሱን ማራቅና በገለልተኛነት መቆም ይጠበቅበታል። የሠራዊቱ አባላት፣ እንደማንኛውም ዜጋ ሁሉ በምርጫ ወቅት የሚፈልጉትን ፓርቲ በመምረጥ የመሳተፍ መብት አላቸው።

ነገር ግን እንደ ሠራዊት፣ እንደ ተቋም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርና ግጭት ውስጥ እጁን በማስገባት ለአንዱ ወይም ለሌላው ድጋፍ መስጠት አይገባውም።

ፓርቲዎቹ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን በመዘንጋት (ወይም አሁን አብይ እያደረገ እንዳለው፣ ሆን ብለው በመጣስ) አገርን፣ ሕዝብን፣ አገራዊ ደህንነትን፣ እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ ሲዳርጉ፣ በሕገመንግስታዊና ሕጋዊ አግባብ ብቻ ጣልቃ በመግባት ፖለቲካዊ እብደቱን ወደ ስክነት እንዲመለስ ጥረት ያደርጋል። ከዚህ በተረፈ፣ ለየትኛውም ፓርቲ የበላይነት ብሎ የሚሠራው ሥራ አይኖረውም።

በማንኛውም ጊዜ፣ የሠራዊቱ ወገንተኝነት፣ ለሕገ-መንግሥቱና በሕገ-መንግሥቱ እውቅናና ዋስትና ለተሰጠው የሕዝቦች መብት፣ ፈቃድና ጥቅም ብቻ ነው።

PS. ሰሞኑን፣ ብርሃኑ ጁላ፣ ሠራዊቱን፣ ሕገ-መንግስትን በመጠበቅ ሥም የአብይ ጠባቂ ለማድረግ የሚያደርገው ንግግርና እንቅስቃሴ፣ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። የአብይ ፖለቲካ ሕገ-ወጥ በሆነው መጠን፣ ብርሃኑ ጁላም በሕገ-ወጥና በወንጀል ተግባር እየተሳተፈ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም፣ የሠራዊቱ ዋና ኤታማጆር ሹም፣ እና ሌሎች የዕዝ ኃላፊዎች በየደረጃቸው፣ ሠራዊቱ በእንደዚህ ዓይነት የወንጀል ተግባር ውስጥ እንዳገባ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል። አሁን ያለው የአብይ ፖለቲካ እብደት፣ የመከላከያ ሠራዊቱን አንድነት በመጉዳት፣ ወደ መከፋፈል እንዳይወስደው መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
By: via Qerro Media Service - QMS

No comments:

Post a Comment

Featured post

Ethiopia’s controversial quest for the sea

https://ift.tt/4t29xJd Ethiopia is famously landlocked. That’s why the ambitious Ethiopian prime minister Abiy Ahmed has long harbored visi...